VISITORS COUNTER


VISITORS COUNTER

Ticker

6/recent/ticker-posts

ከደመና በታች / ክፍል 1

  


ህይወት እንደቀጠለ ነው ፡፡ በጥሩ ወይም በመጥፎ መሃዘን ወይም በደስታ በምቾት ወይም በጉስቁልና ሊሆን ይችላል ብቻ ግን ምድር ላይ እስካለን ድረስ ካለነሱ መኖር የማንችል የሚመስለንን ሰዎች አተንም ቢሆን ህይወት ይቀጥላል ! በርግጥ እየኖረው ላለው ሰው የትኛውም አይነት ህይወት አልጋ ባልጋ አይሆንም ክብደት እና ቅለቱ ግን እንደ የሰዉ መፍትሄ የማፈላለግ አቅም እና የሚፈጥሩ ችግሮችን እንደየምናስተናግድበት መንገድ ይወሠናል፡፡

 አደይም በቀጠለ ህይወቷ ውስጥ መልስ ያላገኘችለትን ጥያቄ እያሰላሰለች ግራ እንደተጋባች ቀን ቀንን እየተካ ወራት አልፈዋል፡፡ ለወላጆቹዋ ብቸኛ ልጅ ስለሆነች ፍቅር እና ትኩረት የሚጋራት አልነበረም ፡፡ በራስ መተማመኗም ከዛ የመጣ ሳይሆን አይቀርም ለሷ ከቤተሰቡዋ ወጪ ህይወት የማይታሰብ ነው፡፡ ለትምህርት ክፍለ ሃገር ስትመደብ የዩኒቨርስቲ ህይወትን መልመድ አቅቷት ቤት ተመልሳ የግል ኮሌጅ የተማረችበትም ዋነኛ ምክንያት ኢሄው ነው፡፡ ለነገሩ እሷም ልክ እንደ ብዙዎቻችን በለመደቻቸው ደግግሞሾች የታጠረ ህይወት ነው ያላት፡፡

 የአባቱዋ ጉዋደኛ አቶ እንቁ እና ባለቤታቸው የወላጅ ወግ ያዩባት አደይ ለየት ባለ ሁኔታ በሁለት እናትና በሁለት አባት ነው ያደገችው ለማለት ያስደፍራል ፡፡ ለጨዋታ እና ቁምነገር አዋቂዋ አደይ ቤተሰቦቿ እና አብሮ አደግ ጓደኞቹዋ ለሱዋ በምንም የማይተኩ የምቾት እና የደስታ ምንጭ ናቸው፡፡

 ታዲያ ያልተጠበቀው ድንገተኛ የአባቱዋ መጥፋት (ሞት )መከሰት አደይን ሌላ ሠው እስክትምስል ድረስ ለውጧታል ፡፡ ጊዜ በገፋ ቁጥር የአባቷን መሞት ከመቀበል አንድ እርምጃ እየራቀች ብትመጣም ጠፍተዋል ወይስ ሞተዋል ….? ሚለው ነገር ለሷ አሁንም ያልተመለሰ ጥያቄ ነው፡፡ አባቷ ከመኖሪያ ቤታቸው ከጠፉ ወይም ከሞቱ አራት ወራት ሆኖዋቸዋል እሷም አራት ወራት ከማንም ባላወራችው ሃሳብ በመብሰልሰል ጠውልጋለች፡፡ ከአባቷ የነበራት ጥብቅ ቅርበትና ፍቅር ፣በሷ የነበራቸው ኩራት       29አመቱዋ ልክ እንደ ህፃን ልጅ በስስት ያዩዋት የነበረው ነገር፣ ደግሞም እንደልጃቸው ሳይሆን እንደ እኩያ ሚያማክሯት እና ለሃሳቧ ቦታ ሰተው የሚሰሟት ፣ከቅርብ ጊዜ ወዲህልጄ ሁሌ ልጅነት የለም እኛ አንቺን በጥሩ እድሜ በመውለዳችን ነው እኩያ ልጅ ያደረስነው መቼ ነው አግብተሽ ወግ የምታሳይን ለኛም እዘኚልን እንጂ…. አያት ሣንሆን አረጀን እኮየሚለው ቀልድ የተቀላቀለበ ምክር ሳይቀር እንደ ፊልም አይምሮዋ እየተመላለሰ ይታያታል ፡፡  

ለነገሩ አቶ ገረመው እንኳንስ እንደሷ ልክ በሌለው ያባትነት ፍቅር ያሳደጉት ይቅርና ማንም የሚያውቃቸው ሰው በሳቸው መሞት ወይም መጥፋት ቀላል የሆነ የሃዘን ስሜት ብቻ ተሰምቶት ሊያልፍ አይችልም ምክንቱም ሰላማዊ እና ጥሩ የሚባሉ ሠው መሆናቸው ነው፡

ሳቋን ፈገግታ እንኳ ሳያስቀር ከፊቷ ላይ የወሰደውም ያንን ደማቅነቷን መስከረም እንዳለፈበት አደይ አበባ ያጠወለገውም ተጫዋችነቷን ለእናቷ እና አቶ እንቁ ስትል ከምታወራቸው ጥቂት ስሜት አልባ ቃላት ውጪ በዝምታ የተካውም አራት ወራት ቀንም ማታም የምታብሰለስለው አውጥታ ለማውራት ድፍረት ያጣችለት ግራ የሚያጋባው የአባቷ መጥፋት ወይም ሞት ነው !

                                       ከ አራት ወራት በፊት

የአደይ እናት ወ/ሮ አዳነች ያክስታቸው ልጅ ልጇን ትድር ስለነበር ሠርግ ተጠርተው ክፍለ ሃገር የምትገኘው ያክስታቸው ልጅ ሀሙስ ማለዳ የሄዱት በጉራጌ ማህበረሰብ ተወላጆች ዘንድ በደማቅ ሁኔታ ለሚከበረው የእነሾሽላ ስርዓት ለመገኘት ከዛም እስከ መልስ ቆይተው እሮብ ወደቤታቸው ሊመለሱ ነበር፡፡

ሠርጉ ቅዳሜም ቢሆን እሁድ የእንሾሽላ ስርዓት የሚደረገው አርብ ማታ ሲሆን ጠላ በእንስራ ተሞልቶ ከድፎ ዳቦ ጋ ይቀርብ ና ከበሮ እየተመታ “እንሾሽላ ያግድልችጎይ ያቦ አዮ ቤለ” እየተባለ የሙሽሪት ወይም የሙሽራው የዘር ሃረግ እየተዘረዘረ የሚወደስበት ከሠርግ ጋ የተያያዘ በሃል ነው፡፡ እዚህ የአያት የቅድማያት የአክስትና ያጎት እንዲሁም በእናትም ባባትም በኩል የሚዛመዱ ባካል እንኳ ለመተያየት ሞት ጊዜ ያልሰጣቸውን ዘመዶች ስም ከተሰበሰበው ሰው ጭብጨባ ና ድምፁ ጎላ ብሎ እንዲሰማ ፀሃይ ሲንቃቃ ከሚከርመው የከበሮ ድምፅ ጋ ሙዚቃውን እየተቀባበሉ እያወጡ ሲያወድሱ መስማት ቋንቋውን ለማይረዳው ሰው እራሱ አንዳች ውርር የሚያረግ ስሜት አለው ፡፡

                   ******* 

አርብ ምሽት አደይ እና አባቷ የወ/ሮ አዳነችን ያለመኖር ለመርሳት በሚመስል ሁኔታ ከ እራት ቡሃላ ቡና አስፈልተው ከአምሳል ጋ ሞቅ ባለ ጨዋታ ቤታቸውን አድምቀውት መሹ 3፡40 ግን ሲሆን ቡናውን አነሳስታ ስለጨረሰች ለመተኛት ተነስተው አደይ ወደ መኝታ ክፍሏ ስትወጣ አባቷ ወደ እንግዳ መኝታ ክፍል መሄድ ሲጀምሩ……

“ምነው አባ ለምን መኝታ ቤት አተኛም ?”ስትላቸው

“ለፀሎት መነሳቴ ስለማይቀር ለሊት ከምወርድ እዚሁ ብተኛ ይሻለኛል” አሉ ወደ እንግዳ መኝታ ክፍሉ እያመሩ የ እንግዳ ክፍሉ እና የፀሎት ቤቱ በር ትይዩ ነው፡፡

“እሺ አባዬ ሠላም እደር “ ብላ ወደክፍሏ ለመግባት ደረጃውን እየወጣች  እንደ ልማዳቸው በሩን ከውስጥ ሲቆልፉት ሰምታ ፈገግ አለች

ኢሄ በር ከውስጥ ቆልፎ የመተኛት ልምድ አብሯቸው የኖረ ነው፡፡ ከአደይ እድሜ በፊት ከማገባታቸውም በፊት ገና 2ኛ አመት ተማሪ በነበሩበት ዘመን ከ አክስታቸው ቤት ወተው ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ አበባ  ቤት ተከራይተው መኖር ሲጀምሩ በ አንድ ቤት ውስጥ ሦስት ሆነው ነበር የሚኖሩት ፡፡ ቤቱ አንድ ሳሎን ፣ አንድ ማብሰያ ክፍል እና ሦስት መኝታ ክፍሎች ነበሩ፡፡ በዛ ቤት ውስጥ የማይጋሩት መኝታ ቤታቸውን ብቻ ስለነበር የግላቸው የሆነውን ነገር ከልብሶቻቸው ጀምሮ የሚስቀምጡት መኝታ ቤታቸው ውስጥ ነበር፡፡

ከአቶ እንቁ ጋርም የተዋወቁት በዚሁ ጊዜ ነው አቶ እንቁ ያኔ ሠራተኛ ስለነበሩ ደሞዛቸውን በመጠቀም  ለቤት ውስጥ ፍጆታ የሚስፈልጋቸውን ብዙ ነገር የሚያሟሉት እሳቸው ነበሩ ፡፡ ሌላኛው አብሯቸው የሚኖረው ልጅ ልክ እንደ አቶ ገረመው ተማሪ ቢሆንም ከቤተሰቦቹ የሚላክለት ገንዘብ ለ አቶ ገረመው እናታቸው ከሚልኩላቸው በግማሽ ያነሰ ከመሆኑም በላይ ከሡ ፍላጎት ጋ ባለመመጣጠኑ በሚፈልገው መጠን ልብስ እና የትምህርት ማቴሪያሎችን ለማሟላት ይቸግረዋል ፡፡     

ጠዋት ሁሉም የየራሳቸውን የመኝታ ክፍል ቆልፈው የሳሎኑ በር ቁልፍ አንድ ብቻ ስለነበር ቀድሞ የመጣ ሰው ከፍቶ እንዲገባ በራፍ ላይ ያለ አትክልት ውስጥ ደብቀውት ይሄዳሉ፡፡ ሲመልሱ ሳሎን ተሰብስበው ያመሹና ለመኝታ አሊያም ለማጥናት ወደየክፍላቸው ይገባሉ፡፡ የመኝታ ክፍሎቹ በሮች በሳሎኑ ዙሪያ የተደረደሩ ስለሆኑ ሳሎን ያለ ሰው የሁሉንም ክፍሎች በር ማየት ይችላል ስለዚህ ሠው ሳሎን ባለ ሰዓት ማንም ወደማንም ክፍል ሊያመራ አይችልም ፡፡ታዲያ ኢሄ የገባው አብሮዋቸው የሚኖረው ልጅ አንድ ቀን እንቅልፍ ሲጥላቸው ጠብቆ ወደ አቶ እነቁ ክፍል ይገባና የተወሰነ ገንዘብ ከኪሳቸው ይሠርቃል…. አቶ እነቁ በነጋታው የገንዘባቸውን መጉደል ቢያቁትም መናገር ስለከበዳቸው ዝምታን መረጡ ፡፡ በዚ የተጀመረ ቀስ በቀስ ከአቶ ገረመውም ከ አቶ እንቁም ክፍል ከገንዘብ ባሻገር እቃዎችም መጥፋት ሲጀምሩ አቶ ገረመው ምን አሳቀቀኝ ይሉና የመኝታ ክፍላቸውን ከውስጥ እየቆለፉ መተኛት ጀመሩ ጥቂት ቀናት ቆይተው አቶ እንቁም የወዳጃቸውን ፈለግ ተከተሉ በዚ ሁኔታ ለ ሁለት አመት አብረው በ አንድ ቤት ኖሩ ፡፡ በመጨረሻም አቶ ገረመው ከአደይ እናት ጋ ለመኖር ወስነው ከዛ ቤት ሲወጡም ጥቂት ጊዜ እንደቆዩ አቶ እንቁም ወ/ሮ አበባን አግብተው ከሚስታቸው ጋ የትዳር ህይወትን በነፃነት ለማጣጣም ከዛ ቤት ወጡ ፡፡ የአቶ እንቁ እና የአቶ ገረመው ወዳጅነት ከዛ ቤት የጀመረ ነው ከልጁ ጋ ግን ጥሩም መጥፎም ሣይነጋገሩ ግንኙነታቸው ከዛ ቤት ከመውጣታቸው ጋ እኩል አበቃ ፡፡ታዲያ አቶ ገረመው በዚያ ጊዜ መፍትሄ ብለው የጀመሩት በር ከውስጥ ቆልፎ የመተኛት ልምድ አብሯቸው ኖሮ አግብተው ወልደውም በር ከውስጥ እይቆለፉ ይተኛሉ ፡፡

ቅዳሜ ጠዋት አደይ ከእንቅልፏ ተነስታ ቁርስ ለመብላት እና ወደ ስራ ለመሄድ ተዘጋጅታ ወደሳሎን ስትወርድ  ሁሉም ነገር እንደተለመደው  ተዘጋጅቶ ነበር የጠበቃት ለወትሮ አባቷ ለቁርስ ቀድመዋት ለስሚገኙ ስታጣቸው ሰራተኛቸው (አምሳልን) ጠርታ

“አባዬ ቀድሞኝ ወጣ እንዴ …..?’’ አለች ግራ ተጋብታ

“አረ አልተነሱም ስራ አይሄዱም መሰለኝ”

“ለምን ?”

“እኔንጃ ትላንት እንኳ አልሄድም አላሉም እንደው ሳይነሱ ቢዘገዩ ነው እንጂ” አደይ ድንግር እንዳላት ልትቀሰቅሳቸው ወደ እንግዳ ክፍሉ ስትሄድ አምሳል እየተከተለቻት  

“……ልትቀሰቅሻቸው ነው አደይዋ … ?” አለች

“አዎ”

“ውይ አደይዋ ሠሞኑን ስራ በዝቶባቸውም አይደል የከረሙ ትንሽ ይተኙ ባክሽ ሌትም ለ ጠሎት እነሳለው ሲሉሽ አልነበር ትንሽ ያረፈዱ እንደው ስራው ምን ይሆናል ብለሽ ነው” ብላ አይን አይኗን እያየች ስትጠብቃት ምንም ሳትመልሰላት ወደ ምግብ ጠረቤዛው ሄዳ ቁርሷን በልታ ሳታገኛቸው ወጣች፡፡ ቢሮዋ እንደገባች በጀመረችው ስራ ተመስጣ ቆይታ 4ሠዓት መሆኑን ስታይ ለ እናቷ ደውላ በናፈቆት እንሾሽላው እንዴት እንዳለፈ ካወሩ ቡሃላ

“አባትሽ ጋ ስደውል አያነሳም ምን ሆኖ ነው ?” ሲሏት  

“ቀድሜው ነው የወጣሁት እንዲደውልልሽ እነግረዋለሁ” ብላ ተሰናብታቸው ስልኩን ዘግታ ለአባቷ መደወል ጀመርች ግን ደጋግማ ብትደውልም ስልካቸው አይነሳም እየደወለች ባልተነሳ ቁጥር ልቧ ምቱ እየፈጠነባት ሲመጣ በ አምሳል ስልክ ስትደውል መጠራት ከመጀመሩ አንስታ……

ይቀጥላል

.

.

.

 

Post a Comment

0 Comments