በእንግድነት ተጠርቼ ከተገኘሁበት የወላጆቼ የቅርብ ወዳጅ የሆኑት ሻንበል ቤት እንደኔው ተጋባዦች ልጆቻቸውን ይዘው ተኝተዋል፡፡ ህፃናቶቹ ቤቱ ውስጥ ከወዲያ ወዲህ እየተሯሯጡ ሲጫወቱ አንዱ ችኩል ታዳጊ በእሩጫው መሀል ከፎቶ መደርደሪያቸው ስፍራ ሲደርስ በዘረጋው እጁ አንዱን የፎቶ ፍሬም በእጁ መቶት አለፈ፡፡ የፍሬሙ መስታወት በዘመናዊ ቤታቸው ላይ ባነጠፉት ምቹ ምንጣፍ ከመሰበር ቢድንም፡፡ የቤቱ አባዎራ ግን እድሜ እና ጤና በገደበው ግዙፍ ሰውነታቸው እየተጣደፉ ሄደው የተበታተበውን ፍሬም አንስተው በስስት ደረታቸው ላይ እንደለጠፉት ተመልሰው ከነበሩበት ስፍራ ተመለሱ፡፡ ለረጅም ጊዜ ሳውቃቸው እጅግ የተረጋጉ ሰው ስለሆኑ ሁኔታቸው ቀልቤን ሳበው እናም በትኩረት ሳስተውላቸው በፍሬም ውስጥ የነበረውን ምስል ቀረብ እራቅ እያደረጉ ሲያስተውሉት ለሰዎች ቦታ ልልቅ በሚል ሰበብ አጠገባቸው ስሄድ እንድቀምጥ ጋበዙኝ ፍላጎቴስ እሱ አልነበር ተቀምጬ የሚመለከቱትን ምስል አብሬ ማየት ጀመርኩ፡፡ ምስሉ ላይ አንዲት የፈረንጅ ልጅ ከፊት ለፊቷ ግርግዳ ላይ ያለ የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ፊት ሻማ ለኩሳ ተንበርክካ ስትፀልይ በጎን የሚያሳይ ነው፡፡
“እንዴት ከቤተስብ ፎቶ ጋር በፍሬም ልትቀመጥ ቻለች” አልኳቸው በፈገግታ
“ታሪክ አላት ከኔ ጋር ብዙ ቆይታለች እስኪ ገምቺ ይኼ ምስል ከኔ ጋር ስንት አመት የሆነው ይመስልሻል” አሉኝ
“እኔንጃ ጋሼ መገመት ይከብዳል" አልኳቸው አንዴ እኔን አንዴ ምስሉን እያፈራረቁ ሲመለከቱ
“በአስራዘጠኝ ሰባ አራት ሰባ አምስት አመተ ምህረት አካባቢ በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል በነበረ ጦርነት ከረን……አስርተ …… ስማጥ ይሚባሉ ስፍራዎች ላይ እየተዋጋን በታጋጋለ ተኩስ መሀል ነው መሬት ላይ ይኽችን ምስል ወድቃ ያገኘሁ እና ያነሳዋት እንግዲህ ያኔ አንቺ አልተወለድሽም” ብላ ፈገግ አሉ፡፡ በየመሀሉ በተደጋጋሚ የተዘጋጀውን ምግብ እንዳነሳ ለሚቀርብልኝ እናታዊ ቁጣ አዘል ትህዛዝ ከመሸነፌ በፊት
“በጣም እረጅም ጊዜ ነው” አልኩ በአይምሮዬ ጊዜውን እያሰላሁ
“አዎ ብዙ ጊዜ ነው የታሪኬ አንድ አካል ነው እኔም ከተሰለፈኩባቸው ጦርነቶች በተደጋጋሚ ከሞት ያመለጥኩበት አጋጣሚ የነበረው ምስሉን ባገኘሁበት ስፍራ ነበር ፡፡ ከዛህም በኋላ በተሰለፍኩባቸው ግንባሮች አብራኝ ተሰልፋለች፡፡” አሉ በኩራት
“42…..43 አመት ማለት እኮ ነው በጣም እረጅም ጊዜ ነው፡፡ ግን ምስሉን ይዞት ወደ ጦር ሜዳ የመጣው ሰው ምን ሆኖ ይሆን የጣላት ባገኙበት ሰፈራ አስክሬን ነበር “አልኳቸው ያነሳሱት ጥያቄ ውሃ እንደማያነሳ እየተሰማኝ ብዙ እንዲያወሩኝ በመጓጓት
“ምንም አልነበረም፡፡ ምናልባት ተማርኮ ሲደርሱበት ጥሎት አልያም ከኪሱ ወድቆበት ይሆናል፡፡ ደግሞም ምስሉ በተጣለበት እና እኔ ባገኘሁበት ወቅት መሀል ያለውን የጊዜ እርቀት በምን ማወቅ ይቻላል ብለሽ ነው ጦርነት መጥፎ ነው፡፡”ብለው ምስሉን ፍሬም ውስጥ ማስገባት ሲጀምሩ ፡፡ ፍቃዳቸውን ጠይቄ በስልኬ ፎቶ አነሳሁት፡፡ እሳቸውም ፍሬሙን ገጣጥመው በይ ተነሽ ምግብ አንሺ ብለውኝ የመጨረሻ ልጃቸው ከእንጊሊዛዊ ነጭ ባሏ ጋር በፈገግታ ከተነሳችው የሰርግ ፎቶ ጎን ወስደው አስቀመጡት፡፡ የኔ ልብ ግን ያ ሰው ማን ይሆን ? ምንስ ሆኖ ይሆን ? እያለ ቀረ ፡፡ የሱ ታሪክ አካል ሆና ጀምራ የእሳቸው የታሪክ አካል ሆና ያገኘኋት በውሃ በማይበላሽ ሻካራ ፕላስቲክ ላይ የታተመቸው ይህቺ ምስልስ የዛሬ 43 አመት ምን አይነት ስፍራ እና ሁኔታ ላይ ትገኝ ይሆን?
በሜሮን መለሰ ሀብተወልድ
2 Comments
ፍቅር፣ ታሪክ፣ ጭንቀት፣ የህይወት መንገድ፣ የሰውነት ቆይታ፣ እና የልብ ግልጽነት በጽሑፉ ውስጥ በተለዋዋጭ መንገድ የተያዩ ናቸው።
ReplyDeleteምስሉ ምን እንደነበረ የሚያውቀው ሰው ሊኖር ይችላል፣ ይሁን እንጂ ይህ ፅሁፍ የሚያስተምረን ነገር የአንድ ነገር እውነተኛነት ብቻ ሳይሆን፣ ታሪኩ እንዴት ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው አስተዋዮች በላይ ልቦና የሚቀስቀስ መሆኑን ያሳያል።
ከልብ አመሰግናለሁ። ከቀን ውሎዬ በአንዱ ያውም ግንቦት 19 /2017 አ.ም በሰአቱ ያስተዋልኩት እና የሰማሁትን እንደወረደ ነው ያሰፈርኩት። ፎቶውም በትክክል ታሪኩን ሲነግሩኝ ያነሳሁት ፎቶ ነው።
Deleteነገር ግን ከዚህ ኮሜንት በኋላ ስለዚህ ምስል ለመረዳት ጎግል ባደረኩበት ጊዜ እንደ ኤሮፕያን የጊዜ ቀመር በ1960 ማለትም ከ65 አመት በፊት በጃፓን እንደተሰራ ለመረዳት ችያለሁ ስለምስሉ መረጃ ያገኘሁት item description from the seller የሚለውን ተጭኜ ነው
https://www.ebay.co.uk/itm/255886239716
ከእለት ተህለት ህይወቴ እንደወረደ የተፃፈ መሆኑን አስቀድሜ ባለመግለፄ ከልብ ይቅርታ እጠይቃለሁ። ለተጨማሪ እውቀት አንድ እርምጃ ላራመደኝ እና ፍፁም ቅንነት ለተሞላበት አስተያየት ፈጣሪ ያክብርልኝ🙏