VISITORS COUNTER


VISITORS COUNTER

Ticker

6/recent/ticker-posts

አዳኝ ጆሮ


 የካፌው በረንዳ ከዝናቡ ውሽንፍር ሊከላከለኝ ስላልቻለ ውስጥ ላሉት ሰዎች ጀርባዬን ሰጥቼ ካፌውን ባጠረው መስታወት አሻግሬ እያየሁ ካፌው ዉስጥ ተቀምጫለው።  ከጀርባዬ አረ እንሂድ የምትል እንስት ድምፅ ደጋግሞ ይሰማኛል፡፡  እሺ እንሄዳለን እያለ ወሬ ሲያስቀጥላት ቆይተዋል ። ልሰማቸው ምንም ጥረት አላደረኩም፡፡ ነገር ግን እኔ ያዘዝኩት የፆም ማኪያቶ እስኪመጣ ሁለት ህልም አውርታለታለች፡፡ ነውር ይሆንብኛል ብዬ እንጂ ምንም የተጨበጠ ነገር የሌለው ህልሟ ውስጥ እነዛህ ሁሉ በስም ለይታ የምታውቃቸው ሰዎች እንዴት እንደታጨቁበት ብታስረዳኝ ደስ ይለኝ ነበር፡፡  እንሂድ የሚል ድምፁዋን ለመጨረሻ ጊዜ ከማሰማቷ ወዲያ ወንበር የመንፏቀቅ ድምፅ ሰማሁ፡፡ እፎይይይይ ግልግል ትከሻዬንም ከብደውኝ ነበር። ለመሄድ መነሳታቸው ደስ አለኝ፡፡

የኔ ወዳጅ እንደሆነ ቀጠሮ የማርፈድ አመል አለበት፡፡ ቢያረፍድም ግን አይቀርም፡፡ ብቻውንም አያረፍድም እሱን ተከትሎ የሚመጣ ለልቤ የማይቀርበኝ ጓደኛውንም አስረፍዶት ነው የሚመጣው፡፡ እኔም ምንም ያህል ሰአት ያስተካከልኩ እና አመቻችቼ የወጣሁ ቢመስለኝም ከመጠበቅ ተርፌ አላውቅም፡፡ የጥንዶቹን መሄድ ተከትለው ጎኔ ባለ ወንበር ላይ ሁለት ወንዶች ተሰየሙ፡፡ “እናልህ…..“ ብሎ ሲጀምር የድምፁ ዜማ ሳበኝ ፡፡  ምን እያወሩ መጥተው ይሆን?  የማወቅ ፍላጎቴ እየናረብኝ “እሺ…..“አለ አድማጩ ሺ የምትለውን ፊደል እንዴት ጎትቶ እንዳዜማት፡፡ ጉድ ለካ ወንዶችም እንዲህ ያወራሉ አልኩ በውስጤ፡፡
“እንዳልኩህ የቆንጆን መስፈርት ታሟላለች፡፡ ደግሞ ስታየኝ የምትሆነው ነገር ፍላጎቷን በቀጥታ ያሳብቅባታል፡፡ እኔም ያው ውስጥ ውስጡን…ሃሃሃ“ ተያይዘው ሲስቁ ላያቸው ጓጓኹ፡፡ እንዴትም እራሴን ተቆጣጥሬ ስልኬን እየነካካሁ መቆየት መረጥኩ
“ ለምን አሳጥረህ እቅጩን አትነግረኝም ተገናኛቹ አልተገናኛችሁም?“ አዳማጩ ድምፅ ውስጥ ሳቅ ተሰማኝ
“ልነግርህ አይደል፡፡ ስልኬን አፈላልጋ ባለፈው ሳምንት ደወለችልኝ፡፡ የማላውቀው ቁጥር ስለነበር የዛህ የእርቅ ጉዳይ መስሎኝ አላነሳሁትም ሲደጋገም ቁጥሩን ቴሌግራም ላይ አስገብቼ ፎቶ አይልሀለው፡፡ የልቤው ጉድ እንዲህ ብላ …..እንዲህ ብላ አላያትም“ እንዴት እያለ እንደሆነ ለማየት ስልኬን ቀና ባረገውም አልታይ አለኝ፡፡ “እኔ ወንድምህ መልሼ ደውዬ እንዳላወኳት ሆኜ አወራኋት፡፡ በጣም ፈልጋኝ እንደነበር ስለነገርችኝ በነጋታው……“ ወሬ ሳይጨርሱ የሚሳሳቁበት መግባቢያ እየታየኝ ስላልሆነ ምንም ደስ  አላለኝም “ሳገኛት ስለኔ ብዙ ነገር እንደምታውቅ ዘርዝራ ነገረቺኝ የሚገርምህ የሁለቱንም ልጆቼን ስም ታውቃለች፡፡ መቼም ፈትቼ እንደማላገባት ቃል በቃል ነግሬያታለው፡፡“
“ታዲያ ምንድነው የምትፈልገው?“ አለ ጠያቂው ከድምፁ ውስጥ ሳቅ ጠፍቶ
“ከ አንድ ወር በኋላ ወደ ውጪ ለትምህርት ትሄዳለች ፓስፖርቷን አሳይታኛለች፡፡  ጥሩ ጊዜ አሳልፋ መሄድ ነው ምትፈልገው“ ድምፁ ውስጥ ኩራት ሲሰማኝ አላስቻለኝም የስልኬን ካሜራ ስከፍት የማርፈድ ምሳሌዎቼ ሳላስተውላቸው አጠገቤ ደርሰው ወንበር እየሳቡ ሰላምታ ጀመሩ በአጋጣሚው ለሰላምታ ተነስቼ ዙሪያውን እንደሚቃኝ ሰው አየት አደረኳቸው፡፡ የሚያማምሩ ሁለት የተመቻቸው ጎልማሶች ናቸው፡፡ ኤጭ አጉል ሰአት መጥተው አስመለጡኝ፡፡ ተደላድለው እንደተቀመጡ ይዘውት የመጡትን ጨዋታ ሲቀጥሉ ጆሮዬን ወደጎረቤቶቼ መለስ ሳደርግ  

“እኔማ ነገ  ስራ አመሻለሁ ብዬ …..አስቤ ነበር፡፡“ ሳቅ እያፈነው እንደሆነ ተዳሁት  “ውዷ ባለቤቴ ደግሞ ነገ እራት ይዘኸኝ ካሎጣህ ሞቼ እገኛለሁ ብላለች፡፡  ሁለት በደልማ አልበድላትም ብዬ እያሰብኩበት ነው“
“ያንተ ታሪክ አያልቅም እኮ ነገም ባይሆን ልጅቷን  ልትበላት ወስነሀላ? “
“ምን ጥያቄ አለው እስካሁንም እኔ ሆኜ ነው አንተ ብትሆን ኢሄኔ …..“ ተያይዘው ሲስቁ አስጠሉኝ፡፡ ምን አይነት የሚያማምሩ ባለጌዎች ናቸው፡፡ ሚስትየው አሳዘነቺኝ፡፡ ባሏ ይወዳታል ፡፡ ሲያወራ እንደበደላት እንደሚያስብ ተናግሯል፡፡ ፍላጎቷን ሊያሟላላት ይፈልጋል፡፡ ያከብራታል፡፡ ግን ሌላ ሴት ጋር ይሄዳል፡፡
“ምን እያየሽ ነው ስልኩ ላይ እንዲህ የተመሰጥሽው“ ብለው ወደስፍራዬ ሲመልሱኝ “የሆነች ፅሁፍ ማንበብ ጀምሬ እኮ……“ ብዬ ስልኬን ወደ ቦርሳዬ አስገብቼ ቀና አልኩ፡፡ ሁሌም በዝምተኝነቴ መታወቄ በጀኝ እንጂ ጆሮዬ ሲያድን የነበረውን ቢያውቁ ሰውም አያደርጉኝ፡፡
 
 
በሜሮን መለሰ ሀብተወልድ  

Post a Comment

3 Comments