የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪም አይደለሁ እኔ ደግሞ በተለየ ሁኔታ ከሜክሲኮ እስከ ካሳንቺስ ያለውን መንገድ አብዝቼ እጠቀማለሁ በምልልሴ ከሜክሲኮ አቅጣጫ ከፌደራል ፖሊስ ከፍል ውሃ እና ከካሳንቺስ አቅጣጫ ደግሞ የቤተ መንግስት ጠባቂ የሆኑ አፍላ ወጣቶች ከኋላው ክፍት በሆነ በኪና ተጭነው አፈሙዛቸውን ወደመሬት ደግነው ሲተላለፉ በብዛት አያለው፡፡
የያዙት መሳርያ ሞት ነው የሚተፋው ባይገድል እንኳን ያቆስላል ስለዚህ ይረብሸኛል። በምንም አይነት ቋንቋ ምንም አያደርግሽም ቢሉኝም አስገዳጅ ካልሆነ በዙሪያዬ ባይኖር እመርጣለሁ ምክንያቴን ብጠየቅ መሳሪያ የሚባለው ብረት ውስጥ ያለው ሞት ስለሆነ ነው ኢሄንን ስል ሞት የምፈራ ሰው አይደለሁም ፡፡ ወደሞት የምንደረደርም ግን አይደለሁም። የሰው ልጅ ከፍቅር ይልቅ ለሞት እና ለፍርሃት ይገዛል የሚል አስተሳሰብ የጦር መሳሪያችን አይነት እያራቀቀው እንደመጣ አስባለሁ፡፡ እንደዚህ ማሰቤን ባሎደውም አንዳንድ ነገሮች ወደድንም ጠላንም እውነትነታቸው አይለውጡም፡፡ ስለዚህም ሰው ከፍቅር በላይ ለፍርሃት እንደሚንበረከክ አምናለሁና የጦር መሳርያ አይኑር አልልም፡፡ ወዳጅ እና ጠላት እስካለ ድረስ ጠላት ሊፈራን እስከተገባም ሞት የሚተፋ ነገር ማስፈለጉ አያስገርምም፡፡
ይልቁኑስ እንደው ዳር ይዞ ግጭት እንደሚያስተውል ሰው በምድርም ሆነ በሃይማኖታዊ ህግ መገዳደል ትክክል ባይሆንም መቼም ጥቅም ያነካካቸው፣ በሀብት ፣በሚስት አልያም በእርስት የተጋጩ ሰዎች ያድርጉት ማለቴ ሳይሆን ቢያንስ እንዲህ ስላደረገኝ ነው ብለው የሚያወሩት ምክንያት አላቸው። ከሁሉ በላይ የሚደንቀኝ በሚልኩት ሞት በከለርም በመልክም በማንነትም የማያውቁትን ሰው በአንድ ባንዲራ ስር ስለተጠለለ አልያም የሆነ ክልል ላይ እና ከሆነ ማህበረሰብ የተገኘ በመሆኑ ብቻ ቤቱ ድረስ ሞት ሲልኩለት ነው ፡፡
ሁለት የሚተዋወቁ መሪዎች የእውነት የሀገርን ጥቅም በማስጠበቅ አልያም በንግግር ሂደታቸው መግባባት ስላልቻሉ ጦርነት ይቀሰቀሳል ያኔ ነገሩ ቶሎ መብረድ ካልቻለ በእግረኛ ወታደሮች የተጀመረ ተንሳፋፊ ሞቶችን ወደመላክ እና ምናልባትም ሀገር ሰላም ብሎ እራት እየበላ ያለ ቤተሰብን፡፡ ስንት ፍዳ አይተው ያሳደጉትን ልጃቸውን መምጣት የሚጠባበቁ ወላጆችን፣ አብሮ ለመኖር ሰርጋቸውን የሚጠብቁ ጥንዶችን፣ ከአመታት ጥናት በኋላ ምርቃቱን የሚጠብቅ ወጣትን ፣ የመውለጃ ቀኗን የምትቆጥ ነብሰጡርን ፣ ምን እየተካሄደ እንደሆነ የማያውቁ ህፃናትን ጭምር ወደማጥፋት ይሻገራል፡፡
በቅርቡ ኢራን እና እስራኤል ሚሲያኤሎችን ሲታኮሱ ተስተውለዋል ኢራኖቹ ማን የሚባል እስራኤላዊ እንደገደሉ ያሳለፈው ህይወት ምን አይነት እንደነበር የእውነትም የላኩት ሞት ይገባው አይገባው ምንም አያውቁም፡፡ እስራላኤላውያኑም ምን አይነት መልክ ያለው ኢራናዊ እንደገደሉ ስንት ቤተሰብ እንደበተኑ ጭራሽ ኢራናዊ ይሁን አይሁንም የላኩለት ሞት የሚገባው ሰው ይሁን አይሁን አያውቁትም፡፡ ምክንያቱም በሃገራት መካከል የሚደረግ ያደገ ጦርነት ዜጋን እና ግለሰብን ሳይሆን ባንዲራን እና የሀገርን ስም ነው የሚያቀው ያህ ተንሳፋፊ ሞት የተላከው እገሌ እና እገሊት ተብለው በስም እና በማንነት ለሚለያዩት ሰዎች መሆኑ ተረስቶ ለዛች ሀገር ይሆናል ፡፡ ሀገር ግን ህዝብ ነው፡፡
በደራሲ እና ጋዜጠኛ ሜሮን መለሰ ሀብተወልድ
4 Comments
🌺❤
ReplyDelete🙏🙏🙏
Deleteሰው ከፍቅር ይልቅ ለሞትና ለፍርሃት ሲንበረከክ ለተንንበረከከለት ዓላማ ተገዢ ይሆናል። ሜሪዬ ለፍቅር እንንበርከክ ብለሻልና እጅሽ ቁርጥማት አይንካው! ❤
ReplyDeleteአሜን እግዚአብሔር ያክብርልኝ
Delete