VISITORS COUNTER


VISITORS COUNTER

Ticker

6/recent/ticker-posts

ስህተትን ለማረም ህይወት የምትሰጠው ድንቅ አጋጣሚ

 


አቶ ገረመው እና ባለቤታቸው በእቅፋቸው ውስጥ የተኛችውን ልጃቸውን ምቾት እንዳይጎልባት እየተጠነቀቁ እና በተሳፈሩበት የህዝብ ማመላለሻ መኪና መስኮት ከመንገዱ ባሻገር እያማተሩ የተራቆቱ እንዲሁም በደን የተሸፈኑ ተራሮችን፣ ንፋስ ከወድያ ወዲህ የሚያዘናጥፋቸው ሰፋፊ የእርሻ ማሳዎችን እያያዩ እና እንዲሁም አልፎ አልፎ እያወሩ ከመጡበት መኪና መናኽሪያ ደርሰው ተወልደው ባደጉበት ስፍራ ወርደው ሲቆሙ ብርክ ብርክ አላቸው፡፡ አይምሯቸውም ብዙ ነገር ያለማቋጥ እያፈራረቀ ማሰብ ጀመረ ክፋቱ ደግሞ አንድም ጥሩ ነገር የሌለው ሃሳብ መሆኑ ነው፡፡

“እናቴ ሞታ ደብቀውኝ ቢሆንስ፣ ዞር በል ከዚህ ብላ ብታባርረኝስ ለነገሩ የክፉ ቀን ቤተሰቦቼን እግዜር ይስጣቸው ለሦስት ቀን ሆቴልም ብንቆይ እንዳንቸገር አርገው ነው የላኩኝ …..ለነገሩ እናቴ ካልተቀበለቺኝማ ሦስት ቀንስ ምን ስናረግ እንቆያለን፣ ስታየኝ እንዳትደነግጥ ለአክስቴ ብነግራት ይሻል ነበር፡፡” እያሉ ያለ ፋታ ሃሳብ በሚያፈራርቀው አእምሯቸው ተወጥረው ዝም እንደተባባሉ ወደ እናታቸው ቤት የሚወስደውን መንገድ እንደተያያዙት በመሃል ባለቤታቸው ጀርባቸውን አሸት አሸት ሲያረጓቸው ከነዚያ ክፉ ሃሳቦቻቸው ተላቀው ፊታቸውን አዙረው ሲያዩዋቸው ወ/ሮ አዳነች በሁለት ዓይኖቻቸው ጠቀስ አድርገዋቸው አይዞህ እንደ ማለት ፈገግ አሉ፡፡ ልክ እንደ መስታወት ያዩትን መልሰው ለባለቤታቸው አሳይተው መንገዳቸውን ቀጠሉ፡፡ አእምሯቸውም ወደቀድሞ ሁኔታው ተመለሰ

“ከዚህ ሁሉ አመት በኋላ ለምን ወደዚህ መጣሁ ? እውነት ህይወቴ ተደላድሎ ለማግባት በወሰንኩበት ወቅት የነበርኩበት ሁኔታ ላይ ብሆን ተመልሼ እመጣ ነበር ? በነዚያ ጊዜያት ያላስተዋልኩትን የእናቴን ናፍቆት የቀሰቀሰብኝ ወላጅ ለመሆን መብቃቴ ይሆን እንዴ?” እያሉ እራሳቸውን በብዙ ጥያቄ እያፋጠጡ እናታቸው ቤት ሲደርሱ እና እየተርበተበቱ ሲገቡ እንባ ተናነቃቸው፡፡

እናታችው አርጅተው ከአልጋ ብዙም የማይነሱ ተነስተው ለመንቀሳቀስም የሰው ድጋፍ የሚፈልጉ ግን ያልተጎሳቆሉ ሆነው ነበር የጠበቋቸው፡፡ ሲገናኙ ተቃቅፈው ተላቀሱ ይኼ በሚሆንበት ሰዓት ወ/ሮ አዳነች ፈርተው እንደሳሎን ባለ ክፍል በር ስር ልጃቸውን አቅፈው ግርግዳ ላይ በፍሬም የተሰቀሉትን ጥቁር እና ነጭ ፎቶዎች እያዩ ማንነታቸውን ሲገምቱ በፎቶዎቹ ብዛት ሲገረሙ እና ቤት ውስጥ ያሉትን ንፅህናቸው ሳይጓደል ዘመን ያለፈባቸውን እቃዎች በአይናቸው እያማተሩ የሚፈጠረውን በጭንቀት እየተጠባበቁ ነበር አቶ ገረመው መኝታ ቤት ገብተው እናታቸውን ያገኙት፡፡ ከናፍቆት ሰላምታው እና ተቃቀፎ መላቀሱ በኋላ

“እሞ እንግዶች ይዤ ነው የመጣሁት መነሳት ትችያለሽ ወይስ እዚህ ይምጡ……?” አሉ የአደይ አባት

“ግድ የለም ከደገፍከኝ እንሳለው” ብለው ቤት ውስጥ ያሉትን የዘመድ ልጆች ተጣርተው ለሁለት ደግፈው ሲያነሷቸው “ተባረኩ በሉ እናንተ ሂዱ እሱ ይደግፈኛል” ብለው ሸኝተዋቸው በልጃቸው ደጋፊነት ሳሎን ደርሰው ሲቀመጡ አቶ ገረመው ባለቤታቸውን እና ልጃቸው እያሳዩ አስተዋውቋቸው ወ/ሮ አዳነች በደንብ እንዲያዩዋት መታቀፊያዋን ገላልጠው የልጅ ልጃቸውን አሳቀፏቸው፡፡ እሞ በሚያለቅሰው አይናቸው አደይን ሲያዩዋት ቆይተው ሦስቴ ቱፍ….ቱፍ…..ቱፍ ብለው ተፉላትና እቅፍ አርግው ሳሟት፡፡ አቶ ገረመውን ቤቱም ሆነ የእናታቸው ሆደባሻነት ሳይቀየር ነበር የጠበቃቸው፡፡ እሞ የልጅ ልጃቸውን አቅፈው ጥቂት እንደቆዩ

“እማማ ታደክሞታለች ልጅቷን ልቀበሎት እና ትንሽ ቆይተው ደግሞ ያቅፏታል” አሉ ወ/ሮ አዳነች በርህራሔ ልጃቸውን እየተቀበሉ

ዝምታ በበዛበት ሁኔታም ቢሆን ከሩቅ እንደመጣ እንግዳ በስርዓት አቀባበል ተደርጎላቸው ተስተናገዱ፡፡ ለነአቶ እንቁም በቤት ስልክ ደውለው ሰላም መድረሳቸውን ነገረው የደረሱት ከሰዓት በኋላ በመሆኑ መስተንግዶ ሲያበቃ መሽቶ የመኝታ ሰዓት እየደረሰ ስለነበር መኝታ ተዘጋጀላቸው፡፡ ያን ቀን እሞ ክፉም ደግም ሳይሉ ስንት ቀን እንደሚቆዩ ጠይቀዋቸው ከመንገድ ስለመጡ እንግዶቹም ቢያርፉ እንደሚሻል እና በደንብ ለመጫወት ጊዜ እንዳላቸው ተናግረው ለመተኛት ገቡ፡፡

ጥንዶቹ ተያይተው በደስታ እና በስጋት ፈገግታ ተለዋውጠው በዝምታ በተዘጋጀላቸው ስፍራ ተኙ፡፡በነጋታው ቁርስ በልተው ጥቂት እንደተጫወቱ ወይዘሮ አዳነች  ትላንት በቅንነትም ቢሆን እሞ በቃኝ ሳይሉ ስለነበር የልጅ ልጃቸውን ከእቅፋቸው የተቀበሏቸው ፀፀት ተሰምቷቸው

“እማማ አሁን ልጆን  ማቀፍ ይፈለጋሉ ልስጦት እንዴ? ” ብለው በፍርሃት በሰለለ ድምፅ ጠየቋቸው፡፡ እሞ ፍላጎት በሞላበት ሁኔታ እራቸውን በአዎንታ ነቀነቁ፡፡ ሲያሳቅፏቸው በድጋሚ እንባ ባቀረረ አይናቸው ሲያዩዋት ቆይተው

“እንዴት ቆንጆ ልጅ ናት? ስሟን ማን አላችሁት?” ብለው አይናቸውን ከህፃኗ ላይ ሳይነቅሉ ሲጠይቁ

“አደይ……” አሉ ሁለቱም እኩል

“እውነትም አደይ… ከከባድ የክረምት ወራት በኋላ የአዲስ ዘመን ጅማሬን የሚያበስር ማራኪ፣ የማይሰለች  እና ተናፍቆ የሚታይ አበባ ነው፡፡ ልክ ሳያት እና ሳቅፋት እንደተሰማኝ ነው ስሟም” ብለው  ቀጠል አርገው “….ግን ምን ነበር እንደዚህ መምጣታቹ ላልቀረ ቀደም ብትሉ? ምን ነበር እንደዚህ ሳልሆን አይኑን እንዳይ ባደረግሽኝ እሱስ ተይው ልቡን አንዳች አደንድኖት ነው፡፡ አንቺ ሴቷ ግን እንዴት ሂድ ብቸኛ እናትህን ጠይቅ አትይውም? ለነገሩ ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለእዳ አይቀበለውም አይደል ተረቱስ፡፡ ሌላው ቢቀር እንዴት ስልክ እንኳ ደውል አትይውም? እስቲ ንገሪኝ  ይኼን ሁሉ ጊዜ የወላድ መካን እንድሆን የፈረድሽብኝ ለምንድነው?” አሉ ወደ ወ/ሮ አዳነች ዞረው፡፡ የአደይ እናት ድንገት የገነፈለ እንባቸውን እየጠራረጉ ከተቀመጡበት ተነስተው እሞ ጉልበት ላይ ተደፍተው

“እማማ ይቅር ይበሉን ምንም በክፋት ያደረግነው ነገር የለም፡፡ እርሶ ትክክል ኖት የእኔም ጥፋት ነው ስልክ እንዲደውል ማረግ ነበረብኝ ግን እማማ እኔም እንደገሬ ቤተሰቦቼን ትቼ ነው ከእሱ ጋር የሆንኩት፡፡ ህይወት አስበን እንደገባንበት ቀላል ስላልሆነልን ነገ ከነገ …ወዲያ… እንዲህ አርጌ ስንል ነው እዚህ የደረስነው ይቅርታ እማማ” አሉ

“አረ በእግዜር ይሁንብሽ አንቺ ልጅ ከእግሬ ላይ ተነሽ ጡር አታሳልፊብኝ እንደው መንገዳቹ ሳተ እንጂ መቼስ የሞቱትን ልጆቼን ተክተሽልኝ ምን አረግሻለሁ በይ ተነሽ” ብለው በአንድ እጃቸው የልጃቸውን ሚስት ትከሻ ደግፈው ቀና ለማረግ እየሞከሩ አደይን ለአባቷ ሰተው ከጉልበታቸው ላይ አንስተው አቅፈው እየሳሟቸው “እኔ ብቸኝነቴ ነው ያስከፋኝ እንባ ማበሻ ይሆነኛል የክፉ ቀን ወዳጆቼን ሰብስቤ አለማችንን እናያለን ፣ መከራዬን አብረውኝ የገፉትን ዘመድ ጎረቤቶቼን ደግሞ በደስታዬ እጠራቸዋለሁ ብዬ አስቤ ስጠብቀው አንድ ልጄ እንደ አልፎ ሂያጅ መንገደኛ በስልክ ላገባ ነው ብሎኝ ሲጠፋ ምን ላድርግ? እኔስ መከታ እና ኩራት ይሆነኛል ብዬ ልጄ ተማር ብዬ ብልከው ያልተማረች እናቱን ንቆ እራሱን ቢድር ነው የከፋኝ፡፡ የምፅናናበት ሌላ ልጅ እንኳ የለኝ፡፡ የኔው ጉድ ሌላ ሃገር ይንከራተታል ቤት ንብረቴን የዘመድ ልጅ ይፈነጭበታል” ሲሉ ወ/ሮ አዳነች አደይን ከአባቷ እየተቀበሉ ድምፃቸውን ዝቅ አርገው “በላ ገሬ” ሲሏቸው በተራቸው ለይቅርታ እናታቸው እግር ላይ ወድቀው እነአቶ እንቁ ገዝተው ያዘጋጁላቸውን ጋቢ አውጥተው ትከሻቸው ላይ ሲያረጉላቸው ከንፁህ ልብ በመነጨ ፍቅር መርቀው ከልብ ይቅር ማለታቸውን እና የልጃቸውን ሚስት እንደተቀበሉ ለማሳየት “አሁን ሴት ልጄ ሆነሽም አይደል በይ ተነሺ እና ቡና  እያፈላሽ የቀረውን እንጫወታለን” አሉ፡፡ ቡናው ቀራርቦ መፈላት ሲጀምር እሞም ጥቄያቸውን ጀመሩ፡፡

“የት ተገናኛቹ አዲስ አበባ ነው የምትኖሪው ?”

“አዎ እማማ ግን እዚህም እንተዋወቅ ነበር አንደኛ ደረጃ ትምህርት የተማርነው አንድ ት/ቤት ነው”

“አሃ… እዚሁ የተጠነሰሰ ነዋ…?”

“አረ በፍፁም አንድ ጊቢ እንማር እንጂ እሱ ስምንተኛ ክፍል እያለ እኔ ስድስተኛ ክፍል ነበርኩ በአይን እንተዋወቅ እንጂ ሰላምታም አልነበረን” አሉ ሃፍረት እያቀረቀሩ

“ለምን አዲስ አበባ ሄድሽ ?”

“በአባቴ ምክንያት ነው ወደዚያ ሙሉ ቤተሰባችን የሄደው”

“እኮ ለምን?”

“አባቴ ለመገላገል ጠብ መሃል ገብቶ የሰው ህይወት አልፎበት 5 አመት ታስሮ ሲወጣ ለሰዎቹ ካሳ ቢሰጥም፤ ሲወጣ ሊገሉት ስለሞከሩ ነው አዲስ አበባ የሄድነው” አሉ መደባበቁ እንደማይጠቅም አስበው

“እንዴት ነው ነገሩ ልጄ ለመገላገል እንዴት ሰው ይገደላል? የአባትሽ ስማ ማነው?” አሉ በጥርጣሬ አይን እያዩዋቸው

“ረዳ ጋሻው ይባላል ያውቁት ይሆናል፡፡ ሰፈራችን ከመናኽሪያው ጀርባ ነው ከዚህ ከሄድን 6 ወይም 7 አመት ቢሆን ነው፡፡ …..የሞተው ሰውዬ ፀቡን እንዲተው ቢገላግሉትም መሃል ቢገቡም አልበርድ ብሎ በጣም ሲያስቸግራቸው አባቴ እንዲሁም ንዴታም ሰው ነው ትእግስቱ አልቆ የብስጭቱን ሰውየውን ሲገፈትረው ወደኋላው ይወድቅና ድንጋይ ይመታዋል፡፡በሰዓቱ አፋፍሰው ህክምና እንዲያገኝ ቢወስዱትም ያንን ቀን አድሮ በማግስቱ ሰውዬው ስለሞተ ነበር አባቴ የታሰረው ሲፈታ ደግሞ ከጥለኛው ጋር ተባብሮ ገደለው ብለው የሟች ቤተሰቦች አቂመው ሊገሉት በመነሳታቸው ምክንያት ያለውን ቤት ንብረት ሸጦ አዲስ አበባ የወሰደን”

“አዬ… ክፉ ቀን የሚያመጣው መዘዝ እኮ ከባድ ነው፡፡ አንድ መጥፎ ቀን የሚያመጣውን መዘዝ 30 ጥሩ ቀን አይመልሰውም እንደው አይፍረድ ነው” አሉ በሃዘኔታ፡፡ የልጃቸውን ሚስት ስርዓት እና ግልጽነት ከነደምግባታቸው ወደውት ነበር፡፡ ለማወቅ የሚፈልጉትን ነገሮች እያከታተሉ ሲጠይቋቸው የአደይ እናት በሃቀኝነት ሲመልሱ አቶ ገረመው በሚስታቸው ላይ የሚደረገውን ምርመራ በዝምታ ሲከታተሉ ቆዩ፡፡ ቀጣዩንም ቀን በጥሩ መቀራረብ እና መግባባት አሳልፈው ተመራርቀው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ፡፡ 

 

                                  ከደመና በታች መፅሐፉ የተወሰደ

 በሜሮን መለሰ ሀብተወልድ

Post a Comment

0 Comments