“ምስጋናው ይቆይ ምክንያቱም ነገ የሚሉንን አናቅም” ብለው ሸኙት በነጋታው እንደተባባሉት ትምህርት ቤቱ በር ላይ ተገናኝተው ወደ ዳይሬክተሩ ቢሮ ሲገቡ አስተማሪው ተጠርቶ ታዲዮስ ላይ የክስ መዓት ያወርድበት ጀመር ገላምጦኛል!……..ንቀት ነው!....... ተውስላልኩት እልህ ነው!….. …….የትምህርት ቤቱን ንብረት ሰብሮዋል!.........መጥፎ አርአያ ነው!....ታዲዮስ ያልተባለው ነገር አልነበረም አቶ ገረመው ክሱ ሲበዛባቸው
“ይቅርታ አርግልኝ እና ይኼን ሁሉ ያረገው ትላንት ነው?” አሉ በፊትም ሲያረገው የኖረው ነገር መስሏቸው
“አዎ!” አለ አስተምሪው በንዴት ጦፎ
“ልጄን ልትከሰው ስለፈለክ በሁሉም ነገር እየወነጀልከው ነው፡፡ እንደሰማሁት ከሆነ ለመክሰስ ካለህ ፍላጎት እንጂ አንተ በገለፅከው መጠን ስህተት ሰርቶ አይመስለኝም፡፡” አሉ አቶ ገረመው እረጋ ብለው በዚህ ንግግራቸው ዳይሬክተሩም ተናደው ለአስተማሪው ተደርበው ሊናገሩ ሲሉ አስቁመዋቸው ለአስተማሪው
“እኔ አሁን አንተን ልከስህ ብፈልግ ተጠርተህ ስትገባ እንደገባህ ከእግር እስከራሳችን ደስ በማይል መልኩ አይተኸናል ይኼ ግልምጫ ነው፡፡……ስታወራ በጣም ጮክ እያልክ ነው እኔ መጠራቴን አክብሬ ስመጣ ጮኸኽብኛል፡፡ …….ገብተህ መናገር ከመጀመርህ በፊት እኔ ማንነቴን ስነግርህ አንተ እራስህን አላስተዋወከኝም ምክንያቱ ደግሞ ንቀት ነው፡፡ በመጨረሻ እነዚህ ያረካቸውን ነገሮች ጠቅለል አርጌ ጥሩ አርአያነት አይደለም ብዬም ልከስህ እችላለው፡፡ ፍላጎታችን መካሰስ ከሆነ ከዚህም በላይ ብዙ ብዙ መዘርዘር ይቻላል ግን ምንም ጥቅም የለውም፡፡ እኔ አሁን ስለተናደድክ ነው ብዬ ስላሰብኩ አሁን ያልኩህን ሁሉ በንዴት ምክንያት እንዳረከው አስቤ አልፌዋለሁ፡፡ አንተም የእኔ ልጅ አደረገ ያልከውን ነገር የእድሜው ተፅህኖ ነው ብለህ ብታልፈው ወደዚህ ሁሉ ክስ አይተነተንም ነበር ተሳሳትኩ እንዴ” ብለው ወደ ዳይሬክተሩ ሲዞሩ ከንዴታቸው ቀዝቀዝ ብለው
“አልተሳሳቱም የታዲዮስ አባት ግን ይኼ ማለት ልጁ ጥፋት የለበትም ማለት አይደለም የሰበረውንም መስታወት ማሰራት ይኖርባቹሃል” አሉ ዳይሬክተሩ
“ልክ ነው ልጄ አላጠፋም አላልኩም እሱም በደንብ ጥፋቱን ያውቃል፡፡ መቼም ቢሆን በድጋሚ እንደዚህ አይነት ስህተት አይሰራም ….ትምህርቱ ላይ እንዴት ነው?”
“ጎበዝ ተማሪያችን ነው” አለ አስተማሪው በሃቀኝነት እና በቁጣ
“ጥሩ ስለዚህ አሁን ተነስተህ አስተማሪህን ይቅርታ ጠይቅ እና ወደ ክፍል ለመግባት ከፈቀደልህ እኔ የቀረውን አስተካክላለው” ሲሉ ታዲዮስ ተነስቶ በስነስርዓት አስተማሪውን ይቅርታ ጠይቆ ወደ መማሪያ ክፍሉ እንዲገባ ተፈቅዶለት ሲሄድ አቶ ገረመው ቆይተው የመስታወቱን ክፍያ ፈፅመው ከአስተማርው ጋር የነበረውን መካረር ለማብረድ “ያለበት እድሜ በጣም ከባድ ነው በዚያ ላይ በአባቱ ሞት ምክንያት ፈታኝ ጊዜ እያሳለፈ ነው ልትረዱት ሞክሩ እኔም በእሱ በኩል ያለውን አስተካክላልው” ብለው ከአስተማሪውም ከዳይሬክተሩም ጋር ይቅርታ ተጠያይቀው እና ተመሰጋግነው በተፈለጉበት ጊዜ ሁሉ እንደሚገኙ ቃል ገብተው ተለያዩ፡፡
ከመፅሐፉ ገፅ 94 የተወሰደ
0 Comments