ስኖር ስኖር የታገስኩት ይደክመኛል

ስኖር ስኖር የከዳኽኝ ቦታ ያመኛል

እሱን ሳልፈው የእናቴ እንባ ይፈጀኛል

ቀን ከለሊት እንዲህ ስትል ይሰማኛል

አንቺስ የቀየው ምሩቅ አድባሯ የታረቀችሽ

ለመካኗ ልጅ ሆነሻት አለቺኝ እሷ ያለችሽ

አይኑ ቢያዝ ምርኩዝ መሪ ለደካማው መደገፊያ

አለችን የምንልሽ ልጅ የሁላችን አይን ማረፊያ

ምነው ልጄ ከዚህ ብኩን ምኑ ጣለሽ

ምርቃትሽን በእርግማን ማን ቀየረሽ

ባፍረት አንገቴ ይደፋ እኔ እናትሽ አይን ይብላኝ

ብላ ደረቷን ስትደቃ ሳይ እንባዬን ውጬውም ከፋኝ  

ምከፋቴን ታውቀዋለህ 

መጎዳቴን ታየዋለህ

እኔ አንዷ ስንቱን ልቻል ስኖር ስኖር የታገስኩት ይደክመኛል

ስበረታ የከዳኻኝ ቦታ ያመኛል

እሱን ሳለፈው መጥፎ ሰዎች አፍገጠሙ ለአሉሽ አሉ

ጉድ ብለው ተዋደዱኝ ሰማህ ሰማሽ ተባባሉ

ስሜ መታረቂያቸው ሆነ ለተጣሉ በመንደሩ

ጨካኝ ክፉ ምህረት አልባ ለወደቀ የማይራሩ

እኔ አንዷ ስንቱን ልቻል ስኖር ስኖር የታገልኩት ይደክመኛል

አለህ ብዬ እያመንኩህ የከዳኸኝ ቦታ ያመኛል

ህመሜ ነህ አንተ ለኔ የልቤ ስርቻ ቁስል

የንፅህናዬ ጉደፍ የሃዘን ዘመኔ ምስል

አንተ ለኔ የእህህ ዜማ መልመጃዬ

ታሞ ታሞ ሲያገግሙ በግርሻ ስቃይ መክረሚያዬ

እኔ አንዷ ስንቱን ልቻል ልኖር የታገልኩት ይደክመኛል

እሱን ችዬም የከዳኸኝ ቦታ ያመኛል

እያረሩ መሳቅ ስማር እያቃሰቱ መፈገግ

ልቤን ደግሞ አደከመው መጨረሻህን መፈለግ

እኔ አንዷ ስንቱን ልቻል ልኖር የታገልኩት ይደክመኛል

እሱን ችዬም የከዳኸኝ ቦታ ያመኛል

                                                         20/10/2018

 

 

                                           ደራሲ እና ጋዜጠኛ ሜሮን መለሰ ሀብተወልድ