ትዝ አለኝ ድንገት አንዱ ከፃፍክልኝ ግጥም መሀል
ወደማለቂያው ሲደርስ ለኔ እና ላንቺ ቤት ይላል
“በሰኞ ማክሰኞ ዘመን በልጅነት ጨዋታ
ያኔ ጀመርኩኝ ቤት መግዛት ለሁለታችን ደስታ
ይሔው ቤትሽ ግቢበት ሁኚበት ልብሽ እንዳሻው
መሄድ ወይም መቆየት ያንቺ ነው እና ድርሻው
ፍቅሬ ግዳጅም አያውቅ ከደስታሽ ምንስ በልጦበት
የልቤ መዝጊያው አንቺ ነሽ ከፍተሸው እንዳትቀሪበት”
አንተ ባልክበት መንገድ እንዴት እንደምል ሲጠፋኝ
ግጥም ባለመቻሌ የምር ዛር ነው የከፋኝ
ስንኝ መቋጠር ብችል እንዳንተ ቃላት ማሳመር
በዘዴ እዘጋው ነበር ልብህ ክፈቱን እንዳይቀር
በጨዋታ ባለፈው ባስታወስከው ልጅነት
መሰረት ተጥሎበታል የኔ እና ያንተ ማንነት
በሰኞ ማክሰኞ ዘመን በልጅነት ጨዋታ
ዋጋ ያስከፍል ነበር መዘናጋት እኮ ላፍታ
መፎረሽም ነበረ፡፡ መባረርም ነበረ፡፡
እያለቀሱ ለምኖ እንቢ መባልም ነበረ፡፡
ጥሩም ስሜት ነበረ ይሕንን ሁሉ የሻረ
ከገዛህልኝ ሰኞ ፎርሼ ስታባርረኝ
ጓደኛህ ነበር ያቀፈኝ አይዞሽ ብሎ ያባበለኝ
መታቀፍ በዛው ለመድኩ የመባበል ሱስ ያዘኝ
ካጣሁት እጅግ የሚበልጥ ብዙ መወደድ አሳየኝ
እግሮቼ መሄድ ለመዱ መላቀስ ያኔ አከተመ
ሁለት ይሻላል ብሎ ሀሙስን ልቤ አለመ
ሀሙስን እሱ ገዛልኝ ቆምኩኝ በሁለት እግሮቼ
የልጅ ልቤም ተፅናናች የተሻለ አጊኝቼ
መፎረሽ አመል ሆኖብኝ ከሱም ብዙ አልከረምኩ
አርብ እና ቅዳሜን ሰጠኝ ወደ ጓደኛው ተሻገርኩ
በጨዋታ ባለፈው ባስታወስከው ልጅነት
መሰረት ተጥሎበታል የኔ እና ያንተ ማንነት
ምናለ አንተን ባረገኝ ቃላት መሰደር በቻልኩኝ
የረሳኸውን ትዝታ እንደዚህ ብዬ በፃፍኩኝ
አንተ ባልክበት መንገድ እንዴት እንደምል ሲጠፋኝ
ግጥም ባለመቻሌ የምር ዛሬ ነው የከፋኝ
በሜሮን መለሰ ሀብተወልድ
0 Comments