ነግቶ አይኑን ለማየት እንቅልፍ ያጣሁለት
መቼ ነው በማለት አመታት ተቆጥረው ቀን የነጎደለት
ሳየው ድንብር ብዬ የረገጥኩት ወጣት
በይቅርታ ብዛት ነብሱን ያስጨነኳት
እቴ የእናቴ ልጅ በልጅነት ዜማ ጠይቂኝ ልንገርሽ
ምን ይደበቅሻል ሚስጥሬ ሚስጥርሽ
እቴሜቴ ስትይ ስል የሎሚ ሽታ
በይኝ ያሰውዬ ምናለሽ ማታ?
ቅኔን በለመደ ቅኝት በበዛነት
በማይጠገበው በቁጥብ አንደበት
ምን አለኝ መሰለሽ ያሰውዬ ማታ
ሁሉን ትውት አርገሽ ረጋ በይ ላንዳፍታ
ብሎ ክንብንቤን ሸብ እያረገልኝ
የዘመናት ህልሜን ባንድ ቃል ፈታልኝ
ምናለኝ መሰለሽ ያሰውዬ ማታ
ለብቻ ታልሞ ለብቻ የተፈታ
ያወቀው ይመስል የውስጤን ጥያቄ
ካፉ ቃል እስኪወጣ ሳየው ተጨንቄ
እህቴ ብሎ ጠርቶ ምንም አይደል አለኝ
ባንድ ጎን ጠግኖ በሌላው ሰበረኝ
ልቤ እሱን ሲመኘው ፍቅር መባል ሽቶ
ማን ይመስክርልኝ በዛች ቅፅበት መጥቶ
ለካ ምንም አይደል መምጣትም መቅረትም
ለካ ምንም አይደል ተቀባይ ከሌለ መለገስ መስጠትም
ለካ ምንም አይደል ለሱ ያለኝኝ ስሜት አግዝፌ ማየቴ
እርብሽ ብሽ ድንግጥግጥ ድንብርንር ማለቴ
ለካ ምንም አይደል ሲያፈቅር የኖረን እህቴ ብሎ መጥራት
ትህትና በሞላው በለሰለሰ ቃል እያፅናኑ መጉዳት
በሜሮን መለሰ ሀብተወልድ
4 Comments
❤️❤️
ReplyDelete🙏🙏🙏🙏
Delete🤗❤
ReplyDelete🙏🙏🙏🙏
Delete