ከወንበሮቹ በአንዱ ከአንዱም ጥግ ላይ  ነጠል ብሎ የተቀምጠው ላይ ናት፡፡ ከወንበሮቹ በአንዱ ከአንዱም ልክ እንደ ምስሶ ከቤቱ ማህል ላይ የተቀመጠውን ጠረዛ ከከበቡት ወንበሮች በአንዱ ላይ ነው፡፡ እኔ ታዛቢዋ ከበረንዳው ወንበሮች በአንዱ ላይ ጀርባዬን ለመንገዱ ሰጥቼ ከጓደኞቼ ጋር ለመመሳሰል ያዘዝኩትን ጣዕም አልባ ሎሚ በሻይ ፉት እያልኩ ካፌው በታጠረበት መስታወት ወደውስጥ ሁኔታቸውን እከታተላለሁ፡፡ እውነት ለመናገር ከሁለቱ ሰዎች ውጪ ሌሎች ጠረቤዛዎች ላይ ሰዎች አሉ፡፡ 
 
አይኖቼ ግን ሁለቱን ሰዎች ሰረቅ አድርገው ሲተያዩ እጅ ከፍንጅ ያዛቸው፡፡ መተያየታቸው እኮ ላይገርም ይችላል እሺ ምን አስገነገጣቸው ? እሺ መደንገጣቸው ይሁን የልጅቷ ሽኩርምሚት የበዛበት ፈገግታ እንኳንስ ብቻውን  ቴብል ሞልቶ የተቀመጠን ሸበላ ቀርቶ የኔንም ቀልብ ስቦታል፡፡ አይኖቿን ሰበር አንገቷን ዘመም አድርጋ ስልኳን መነካካት ጀመረች፡፡ እሱስ መች በዚህ ሊያቆም ጭራሽ በስልኩ አድፍጦ ጥርሶቹ ባልተገለጡበት ፈገግታ ቀና ማለቷን  በግንባሩ እያየ ይጠባበቃል፡፡ ደግሞ እንዴት ያለ አመቺ ቦታ ላይ እንደተቀመጠኩ፡፡ እያንዳንዷ እንቅስቃሴያቸው ከእይታዬ አያመልጥም ፡፡ ትንሽ ቀና እንደማለት ብላ ጨርፋ አየችው እመኚ አይሽዋል ደግሞ ቀናያልሽው እራሱ እሱን ለማየት ነው ብላት ደስ ባለኝ ነበር እሷ ሆዬ አንተን ለማየት አይደለም አይነት ዙሪያዋን ቃኝታ አላስፈላጊ መኮሳተር ገበረች፡፡ ሳይታወቀኝ ፈገግ ስል
 
 “…..አይደል ?” አለኝ በስተቀኜ የተቀመጠው ጓደኛዬ ሁሌ ለነሱ መሃል ላይ ተቀምጦ መመስከር ስልች ብሎኛል፡፡ በዛ ላይ የኔ ምስክርነት ምንም ቢሆን በሚያወሩት እርህስ ላይ ለውጥ እንደማያመጣ አሳምሬ ስለማውቅ ያሉትን ሳልሰማ  እራሴን በአዎንታ ነቀነቅኩላቸው፡፡
 
 “እኮ…” ሲል ሰምቸዋለው ነገር ግን ቀጥሎ የተባባሉትን ከመስማት የሚበልጥ ትህይንት በሸበላው ተደረገ እጆቹን የመንጠራራት ያህል ዘርግቶ አስተናጋጅ በምልክት ጠራ  ፡፡ ደበረኝ እውነት ደበረኝ ምናለበት ግን ትንሽ ቢቆይ መች እኔ ብቻ እሷም ድንገት ፊቷ ወደቀባት እና ተጋፍጣ ታየው ጀመር፡፡ አቤት መሯሯጥ ደግሞ የአስተኛጋጇ ፍጥነት ….. ጭራሽ ተጠጋችው ….እርፍ ጭራሽ መሳሳቅ ምን ብሏት ይሆን ? ብዬ ሳልጨርስ ጎንበስ አለች በጆሮዋ ወደ ልጅቷ እያየ የሆነ ነገረ አላት፡፡  ኦኦኦ ኢሄ ሰው ጨዋታ ያውቃል ፡፡ ወደ እሷ እያየ እንደሆነ ስታውቅ በወንበሯ ላይ ተደላድላ የመጀመሪያውን አይነት ፈገግታ ለገሰች፡፡ ውስጤ በሳቅ እና መሽኮርመም ሲሞላ ተሰማኝ፡፡ አፍረት በመፈላለግ እየተሸነፈ እየመጣ ነው፡፡
 
አስተናጋጇ በፈገግታ በመጣችበት ቅልጥፍና ባዶ ያደረገውን የማኪያቶ ሲኒ ይዛ ተመለሰች፡፡ እሱም ፊት ለፊት አነጣጥሮ ለሽኩርምሚታም ፈገግታዋ  በሚስቁ አይኖቹ ጭንቅላቱን ግራ እና ቀኝ በመጠኑ…. በመጠኑም ሳይሆን በጣም በትንሹ ምናልባትም ለሌላ ሰው በማይገባ መልኩ አነቃንቆ አይደልልልልል….አይነት ነገር ብሏታል፡፡ እውነት ብሏታል በደንብ አይቼዋለሁ አፍረት ነጥብ እየጣለ ነው፡፡ ጎላ ያሉ አይኖቿን በዝግታ ከድና ገለጠቻቸው፡፡ እየተባባሰ……ነጣ ያለ እጅጌ ጉርድ ሸሚዙን ኮሊታ በሁለት እጁ አስተካክሎ ወደስልኩ ሲያጎነብስ ቀረፃ ላይ ናቸው እንዴ ብዬ ለቅፅበት አሰብኩ፡፡ መቼም ኢሄን ያክል እረጅም ሲን ከት ሳይባል አይቀጥሉም፡፡ ሸበላው ግን እዚህ ጋር ቀሽም ሆነ ልጅቷን ከሙድ አወጣት እኔንም አበሳጨኝ፡፡ ቆጣ ብላ በእጇ የፅሁፍ ምልክት እሱ ለጠራት አስተናጋጅ አሳየቻት፡፡ እባክሽ ትንሽ ተረጋጊ እንጂ ልጅት በጣም እያስታወቀብሽ እኮ ነው ደግነቱ አስተናጋጇ ጭንቅላቷን በፈገግታ ነቅንቃ እሺታዋን ገልፃ ወደ ሌላ ጥሪዋ ሄደች፡፡
 
 ተይ እንጂ አይነት ነገር አላት በአይኑ ፈርጣማ እጆቹ የሞሉት እጅጌ ውስጥ ጣቶቹን ለመክተት እያታገለ በእግረ መንገድም የራሱን እጅ ለዘብ አርጎ እያሻሸ፡፡ እሺ አሁን አንገቷን ሰገግ አድርጋ አይኖቿን አጥብባ ማየቱን ምን አመጣው፡፡ እሰይ የኔ ቀብራራ እሱስ የፈለገው ኢሄንኑ አይደል ወደኋላው ለጠጥ ብሎ ጥርሶቹን አሳያት እኔ ለዚህስ ቃልም የለኝ፡፡ አስተናጋጇ አንድ ቁራጭ ቴራሚሶ ኬክ ከብዙ ፈገግታ ጋር ጠዛዋ ላይ አስቀምጣላት ወደሸበላው እያየች በጆሮዋ አውርታት ሄደች፡፡ እዚህ ጋር ነገር ተቀየረ አቤት ሹካ አያያዝ  አቤት ኬክ አቆራረስ አቤት አስተያየት አቤት አጎራረስ፡፡ አነጀሊና ጁሊ ምን ትተውናለች ደግሞ ሁኔታዋ ሁሉ ጨዋነት የሞላበት መሆኑስ አይኖቿ ከሱ ላይ ሳይነቀሉ ማድረግ መቻሏስ፡፡
 
 ጅንኑ እንደዛው ዘና ብሎ እንደተደገፈ እያያት አንድ ሰው ከየት መጣ ሳልለው መጥቶ ያካለበው ጀመር አስተናጋጇም እንደተማከረ ሰው ከላባው  ሁለቱ ተፈላላጊዎች መሃል እንደቆመ ሳይቀመጥ  ቢሉን ይዛለት መጣች ገንዘብ አስቀምጠው በጥድፊያ እየወጡ ዞር ብሎ አያት እሷም ስታየው የሁለቱም ደስታ ከሽፎ እንደነበር እኔ ምስክር ነኝ ፡፡ አላስችል ያለኝ እኔ ግን በአጠገቤ ሲያልፍ  “እና በቃ….?” አልኩት ፊቴን ወደሱ አዙሬ…..ታዛቢ እንደነበረበት ሲረዳ በአፍረት አጎንብሶ እየሳቀ የፍጥነት እርምጃውን ቀጠለ፡፡  ሰው እንዴት በቅፅበት ሙሉ ህይወት ይኖራል ተያዩ ፣ ተፈቃቀዱ ፣ ተገባበዙ፣ ተናደደች እሱም አባበላት ፣ ልሂድ ስትል አባብሎ አስቀራት፡፡ በቅፅበጽ ያለምንም ቃላት የዘመናትን እድሜ ሲኖሩ ቆይተው በመሃላቸው ጣልቃ የገባው ከላባ ለያያቸው እኔ ደግሞ ነገር አለሙን እረስቼ እነሱን ሳኗኑር መቆየቴ ፡፡ እንግዲህ ደግሞ ያገናኛቹህ እንጂ ሌላ ምን ይባላል፡፡ 
 

በደራሲ እና ጋዜጠኛ ሜሮን መለሰ ሀብተወልድ