VISITORS COUNTER


VISITORS COUNTER

Ticker

6/recent/ticker-posts

Ye atamo dimts / የአታሞ ድምፅ


“በድሮ ጊዜ አንድ በጣም ከበርቴ ሰው ነበር አሉ፡፡”ብለው ትረካቸውን ጀመሩ “ለሃብቱ እና ለደግነቱ ወደር የማይገኝለት ለጋስ ደግሶ ማብላት እንደሱ የተባለለትም ነበር፡፡ የኋላ ኋላ ቀስ በቀስ ሃብቱም ንብረቱም የት ገባ ሳይባል አንድ አንድ እያለ ያለውን ሁሉ እያጣ መጣ፡፡ የችግሩን ፅናት ሲያዩ አገልጋዮቹም እየከዱት መሄድ ጀመሩ፡፡ ሃብቱ እና ንብረቱን ሁሉ ሲጨርስ የቀሩት ሚስቱ እና አንድ እስከሞት አልከዳህም ያለ ታማኝ አገልጋዩ እንዲሁም በደጉ ጊዜ በየሰበቡ ዳስ እየተጣለ የሚደረጉ ድግሶችን ለማድመቅ የሚጠቀሙበት አንድ አታሞ (ከበሮ መሰል የሙዚቃ መሳሪያ) ብቻ እንደሆነ ሲያይ ለሚስቱ እና ለአገልጋዩ መሰደድ እንዳለባቸው ይነግሯቸው እና ያንን አታሞ ይዘው ሦስቱ ሰዎች በየእለቱ የቻሉትን እርቀት ያህል በእግራቸው እየተጓዙ ጀንበር ስታዘቀዝቅ የመሸብን መንገደኞች ነን እያሉ በመንገዳቸው ያገኙት ሰው ቤት እያደሩ በያረፉበትም ያገኙትን ቁራሽ እየቀመሱ ይጓዛሉ፡፡ ከቤታቸው በራቁ ቁጥር ግን የሰው ፊት ማየቱ እየከበዳቸው ሲመጣ የሚቀማምሱትን ነገር ብቻ ሰው ማስቸገር በቂ ነው ብለው በመንገዳቸው ባገኙት ጫካ ውስጥ መኖሪያቸውን ቀይሰው እሳት አንድደው እየሞቁ ማደር ይጀምራሉ፡፡ታዲያ ጨለማን ተገን አድርገው የዱር አራዊቶች ሲመጡባቸውም ይዘውት የወጡትን አታሞ ከደረቅ የዛፍ ቅርንጫፍ ባበጁት መምቻ…..ድድም ….ድድም ..ድድም እያደረጉ ሲጎስሙት ፈርተው ይሸሹዋቸዋል፡፡ እነሱም ውሎእያደር እንደመዝናኛ እየቆጠሩት በተራ በተራ ዜማ እያወጡ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንደሚባለው አንድም አራዊቶቹን ሌላም ድብርታቸውን ያባርሩ ነበር፡፡ ከዛህማ በየምሽቱ የሚመታውን የአታሞ ድምፅ የሚሰሙት የአካባቢው ሰዎች ስለምንነቱ ሲገረሙ እና እርስ በራሳቸው ሲያወሩ ወሬው መልክ ቀይሮ እዚህ ጫካ ውስጥ ከሩቅ የመጣ ጠንቋይ አለ፡፡ የማያውቀው ነገር የለም፡፡ እየተባለ እየተጋነነ መወራት ጀመረ፡፡ በመጨረሻም በከተማው ትኖር የነበረች አንዲት መካን ባለሃብት ሴት እውነት እንደምትሉት ይህ ሰው ሁሉን ያውቅ እንደሆን ሄጅ እፈትነዋለሁ እውነቱን ካወቀ የሃብቴ ወራሽ ይሆናል፡፡ ትልና ሆዷ ላይ እንቅብ አርጋ በመቀነት አስራ እርጉዝ በመምሰል ወደሰውዬው ስትሄድ አገልጋዩ ወገቧ ጋር በተፈታ የቀሚሷ ስፌት ሆዷ ላይ ያደረገችውን እንቅብ አይቶት ኖሮ ለጌታው ይነግራል፡፡ ሃብቱን ያጣው ሰው ደግሞ ቀድሞም ያልሆነውን ነህ ሲሉት አዎ ነኝ ብሎ ነበር እና ሴቲቱ ወደ እርሱ ስትመጣ አገልጋዩን በል ምታልኝ ብሎት፡፡ ድድም….ድድም ….ድድም …በሚለው የአታሞ ድምፅ እና በአገልጋዩ እህህህ…..ህህ… የሚል እንጉርጉሮ ታጅቦ ድምፁን ዘለግ ያደርግ እና

               ሳለሁ በክብሬ ላይ ሳለው በእርስቴ

               ማንጠርጠሪያ ስፌት ነበር ከማጀቴ

ብሎ ቁጭት በሚመስል ሁኔታ እራሱን ከግራ ወደቀኝ ሲያወዛውዝ አገልጋዩ  የጌታውን ተረት የሚመስል የኑሮ ለውጥ አስቦ በቁጭት እና በብሶት ድምፁ እየተሻከረ እንጉርጉሮውን ቀጠል፡፡ ጌታውም በተቀመጠበት እራሱን በእርጋታ ከግራ ወደቀኝ እያወዛወዘ ያቆመውን ዜማ …..

                መልሱት መልሱት መልሱት ከቦታው

             ዛሬስ ከምን ጣለኝ ይህ እግሬ ከርታታው

             ይህ እግሬ ከርታታው ዛሬስ ከምን ጣለኝ

             እንቅብ ከቀሚስ ስር ተቀምጦ የሚያሳየኝ

ብሎ ከአገልጋዩ እና ከሚመታው አታሞ በሚወጡ ድምፆች ታጅቦ የሴትየዋን ፈተና አልፎ የንብረቷ ወራሽ ለመሆን በቃ ከዛህ የጉስቁልና ህይወትም ተገላገለ፡፡ብላ ስታወራ የሰማኋትን አስታወስሺኝ” 

                                               ከመፅሐፉ የተወሰደ

 

 

Post a Comment

2 Comments

  1. ዌብ ሳይት ያለው ደራሲ አገሬ ይኖራታል ብዬ አስቤም አላውቅም:: መፅሃፍሽን እያጣጣምኩት ነው:: ስጨርሰው ከዚህ ቀደም ያሳተምሻቸውን መጽሃፍት ላነብ ጓጓሁ። እና አሳውቂኝ

    ReplyDelete
    Replies
    1. በጣም አመሰግናለሁ ። ኢሄ የመጀመሪያ መፅሐፌ ነው

      Delete