VISITORS COUNTER


VISITORS COUNTER

Ticker

6/recent/ticker-posts

ከደመና በታች


“በቃ ሰላም እደሪ ደክሞኛል” አለ በተከፋ ድምፅ

“ደህና ነህ ግን አሮን ለምንድነው ልትዘጋው የቸኮልከው?”

“ስለደከመኝ”

“ምንድነው እንደዚህ ያደከመህ?”

“አንቺን መፈለግ! ….ለእኔ ስሜት እስኪኖርሽ መጠበቅ!….. ቅዳሜም እደውላለሁ ስላልሺኝ ጠብቄሽ ነበር”

“ጊዜ ስላላገኘው ነው እኮ”

“ቤት አልደወልሽም?”

“ቤትማ ደውያለሁ”

“ያኔ ጊዜ ነበረሽ?”

“ተው እንጂ ለእነሡ የማሳወቅ ግዴታ አለብኝ እኮ”

“ልክ ነሽ!”

“ይቅርታ”

“ቢያንስ ቴክስት ታረጊልኛለሽ ብዬ ጠብቄ ነበር፡፡ በፊት ስላልተቀራረብን እና ስለማታውቂኝ ለእኔ ግድ የሌለሽ ይመስለኝ ነበር፡፡ አሁን እንደዚያ እንዳልሆነ ገብቶኛል 3 እና 4 ወራት ስናወራ ቆይተን እንኳን ነገ እሄዳለው ብለሽ ነው የነገርሺኝ እሺ እሱ ይሁን፡፡ ከጓደኞችሽ ጋር ስለሆንሽ ብቻ ለእኔ ጊዜ አልነበረሽም ወይም ትዝ አላልኩሽም ይኼም ይሁን ትላንትስ ለምን ዝም አልሺኝ?”

“እኔን ለመቀየም ተዘጋጅተህ ከምትጠብቀኝ ለምን አልደወልክልኝም?”

“ጠይቄሽ እንደምትደውይልኝ ነግረሺኝ ስለነበር!”

“ምን እንደምልህ አላውቅም”

“ምንም ማለት አይጠበቅብሽም አደይ ምንም አትበይ፡፡ አሁን ምንም ተስፋ የማረግበት ነገር የለም ይኼ በጭራሽ ሊሆን የማይችል እና ስም የሌለው ግንኙነት ነው፡፡ በፊትም ቢሆን እኔ ነበርኩ ስጠብቅሽ፣ ስትናፍቂኝ፣ ካንቺ ጋር መሆን ስመኝ የነበርኩት፡፡ እኔ ነበርኩ ያፈቀርኩሽ በተገናኘን እና በተደዋወልን ቁጥር በጊዜ ሂደት እኔ ብቻ እንደሆንኩ ይኼ ሁሉ ሲሰማኝ የኖርኩት እረስቼው ነበር፡፡ አሁን እንኳን ስልኩን ሳነሳው እንደናፈቀ ሰው ታወሪኛለሽ ብዬ ጠብቄ ነበር….. በአንቺ ጉዳይ እራሴን እያሞኘውት ነው፡፡

“ይኼን ያህል?”

“ቆይ የእኔ ቦታ የቱ ጋር ነው? ንገሪኝ እስቲ ምንሽ ነኝ?” አደይ መልስ አጥታ ዝም ብላ ስትቆይ “አየሽ ለዚህ ነው ተስፋ የቆረጥኩት…..” አለ በመሰልቸት

“በጣም ይቅርታ ይኼን ያህል ያስከፋሃል ብዬ አላሰብኩም ነበር”

በረጅሙ ተንፈሶ “ምንም አልገባሽም እኮ አዲ” አለ

“ልክ ነህ መደወል ወይ ቴክስት ማረግ ነበረብኝ፡፡ ትላንት እንደገባሁ እንቅልፍ ወስዶኝ ነው፡፡ በርግጥ ምክንያት እንደማይሆን አውቃለሁ አሁንስ ቢሆን እኔ አይደለሁ የደወልኩት? ይኼን ያህል የምትጠብቀኝ ስላልመሰለኝ ነው በጣም ይቅርታ”

“እኔ እያልኩ ያለሁት ከዚህ ሁሉ ጊዜም በኋላ እኔ ስለምጠብቅሽ ብቻ ነው ወይ መደወል ያለብሽ ነው? ይኼን ያህል ከተቀራረብን እና ካወራን በኋላ ልናፍቅሽ አይገባም? ልታወሪኝ መፈለግ የለብሽም? ሌላው ቢቀር በምናወራበት ሰዓት የሆነ ስሜት ሊሰማሽ አይገባም? እኔስ አንድ ቀን ተፈላጊ  ስለመሆን እያሰብኩ መኖር ያለብኝ እስከመቼ ነው? ከጓደኞችሽ ተደብቀሽ የምታወሪኝስ እስከመቼ ነው? በቀረብኩሽ ቁጥር እየወደድኩሽ እና እየፈለኩሽ ነው፡፡ ግን መጨረሻው ለማይታወቅ ነገር ከዚህ በላይ መሄድ ጉዳት ማትረፍ ነው ለማንኛውም ሰላም እደሪ”

“በቃ….?” አለች አደይ በጣም አዝና

“…..እኔንጃ አዲ”

“እሺ ምናልባት ተናደህብኝ ይሆናል ነገ እናወራለን”

“ስለምን ? ስለምንድነው የምናወራው?”

“እኔንጃ….ዛሬ እኮ ሌላ ሰው ሆንክብኝ”

“ተሣስቻለሁ?”

“ምንም አልተሳሳትክም ግን እንደዚህ እናወራለን ብዬ አልጠበኩም “

“እስቲ ለእኔ ያለሽን ትክክለኛ ስሜት ንገሪኝ?” አሁንም መልስ አጥታ ዝም አለች

“እሺ በዚህ ሁኔታ እንድቆይ የሚያረገኝ አንድ ምክንያት ንገሪኝ”

“በምን ምክንያት ነበር የወደድክኝ?”

“አብረን እንሆናለን ስንቀራረብ ለእኔ ያለሽ ስሜት ይቀየራል በሚል ተስፋ”

“በሁለት ቀን በሚያበቃ ተስፋ?”

“ተሣስተሻል በሁለት ቀን አረጋገጥኩ እንጂ በእያንዳንዱ ቀን ሳስበው ነበር፡፡

“ከዚህ በላይ ምንም ማለት አልችልም”

“እሺ ሰላም እደሪ” ብሏት ስልኩን ጆሮዋ ላይ ዘጋው፡፡ የተዘጋውን ስልክ ስታየው ቆይታ ቁጣው ሲበርድለት ማውራት እንችላለን ብላ አስባ ስልኳን አስቀምጣ ተኛች፡፡ በነጋታው ቀንም ማታም ብትደውልለት አያነሳም፡፡ በተከታታይ ለ4 ቀናት ያወሩበት በነበረው ሰአት ስትደውልለትም ምላሽ አልሰጣትም፡፡ በ 5ኛው ቀን ስልኩን ሳያነሳ ሲቀር “ሃይ አሮን ይኼን ያክል እንዳስቀየምኩህ አላሰብኩም ነበር ከዚህ በላይ ግን ልደውልልህ አልፈልግም ለማውራት ዝግጁ ስትሆን ደውልልኝ” የሚል የፅሁፍ መልህክት ላከችለት ለመልህክቷም ሳይመልስላት ቀረ፡፡

እየደወለች ባላነሳው ቁጥር ለእሱ ያላት ፍላጎት እየጨመረ እና የሆነ ነገር እንዳጣች እየተሰማት ነበር፡፡ ጭራሽ የላከችለትን የፅሁፍ መልህክት ሳይመልስላት ሲቀር እሱን ለማናገር እና ለማግኘት ያላት ፍላጎት በድንገት ጣራ ነካ “ለምን ላኩለት? ምናልባት ባልክለት ደጋግሜ የመደወል እድል ይኖረኝ ነበር….. በመሃል ሊያነሳውም ይችል ነበር” አለች ለእራሷ፡፡ ትንሽ ቆየት ብላ ስልኳን አየችው አልደወለም፡፡ የላከውም መልህክት የለም፡፡ ለሊት ሳይቀር ከእንቅልፏ ሁለት ሦስት ጊዜ እየነቃች ስልኳን አየችው ምንም አልነበረም፡፡ ቀንም ማታም ሃሳቧ አሮን ሆነ ላለመደወል ኩራት ላለመተው ፍላጎት በሁለት ተቃራኒ አቅጣጫ ወጥሯት የእሱን ስልክ በመጠባበቅ ሳምንታት አለፉ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያመጣችው ስልኳን ቶሎ ቶሎ የማየት ልምድ ያስገረማቸው ወ/ሮ አዳነች

“አዲዬ ምንድነው ከስልክሽ ጋር እንደዚህ ያዋደደሽ ሁለት…. ሦስት ሳምንት ሆነሽ እኮ” አሉ

“ሰዓት እኮ ለማየት ነው እማ”

“አሃ….ነው እንዴ …”አሉ ሳቅ እያፈናቸው

“ምን እያልሽ ነው?”

“ሃሃሃሃሃ…..ምን አልኩ አሁን?”

“በጣም እየተከታተልሺኝ ነው እንጂ ምንም አላልሽም” አለች ጊዜውን ማወቃቸው አስደንግጧት

“ሃሃሃሃሃ…. ደጋግመሽ ስታረጊው ትኩረቴን ስበሽው ነው እንጂ ተከታትዬሽ አይደለም” ሲሉ አደይ ስልኳን አንስታ አይታ አስቀመጠችው፡፡ ወ/ሮ አዳነች በጣም ስቀው “ስንት ደቂቃ እንዳወራን ለማየት ነው አይደል አሁንም ስልክሽን ያየሽው? እናት እኮ ልጇን ትረዳለች …….ሃሃሃሃሃ” ብለው ሳቁ

“በቃ ክፍሌ ብገባ ይሻላል” ብላ ተነሳች

“ሃሃሃሃሃ….እሺ ትቻለው ቁጭ በይ”

“ብተኛ ይሻለኛል እማዬ”

“ምንድነው በዚህ ሰዓት የምያስተኛሽ በይ ቁጭ በይ” ብለው ሲያፈጡባት መልሳ ስትቀመጥ “የሆንሽው ነገር አለ እንዴ?” አሉ

“ምን ሆንኩ እማዬ?”

“እንደ በፊትሽ አይደለሽም”

“ምንም አልሆንኩም ትንሽ ስራ በዝቷል ….ድካም ይሆናል”

“ታዲያ የምትሰሪው ለእራስሽ ስራ ሲበዛ ገቢሽ ይጨምራል ደስታሽን ምን አጠፋው? ካልሆነ ሰራተኛ ጨምረሽ እረፍት አድርጊ ሌላም ችግር ከሆነም መፍትሄ የሌለው ምንም ነገር አይኖርም”

“እሺ እናቴ ያን ያህልም አይደለም እኔ የሚያዙትን እቃ በስርዓት እየላኩላቸው ለሁለተኛ ዙር ደረጃውን ያልጠበቀ እቃ ልከውልኝ እሱም አስደብሮኝ ነው” ብላ በአየር ላይ ሳመቻቸው፡፡

ለመተኛት ክፍሏ ስትገባ እንባ ተናነቃት “ምን እየሆንሽ ነው አደይ?” አለች ለእራሷ፡፡ ከአሮን ጋር በምታወራበት እና በሚገናኙበት ጊዜ ከእሱ ጋር በነበራት ግንኙነት ደስተኛ እንደነበረች እራሱ አስተውላው አታውቅም፡፡ ላናወራ የምንችልበት ጊዜ ሊመጣ ይችላል ብላ አስባም አታውቅም፡፡ እሷ ታውቅ የነበረው አንድ ነገር እያወሩ እና እየተገናኙ መሆኑ ምቾት እየነሳት እንዳልሆነ ብቻ ነበር፡፡ እናቷ ዛሬ ባይናገሯት ኖሮ መሸነፏን ላለማመን እያረገች የነበረው ጥረት ከንቱ እንደቀረ አታስብም ነበር፡፡ አልጋዋ ላይ ትራሷን አቅፋ ቁጭ ብላ ፊት ለፊቷ አልጋው ላይ የተቀመጠውን ስልክ እያየች ልክ እንደሰው ታወራለት ጀመር፡፡ “በጣም መጥፎ ሰው ነው፡፡ እኔ ለእሱ ጥሩ ስሜት በሌለኝ ጊዜ እንኳን ሲደውል እያነሳው ሳናግረው እና ሳገኘው አልነበር? ወይስ ስንቀራረብ እሱ ሲያስበኝ ከኖረው አንሼ ታየውት?” ድምፁዋ እየሻከረ እና እንባ እየተናነቃት “በዚያች አጭር ደቂቃ ውስጥ በአንዴ ብዙ ጥያቄ ነው የጠየቀኝ፡፡ የቱን ምን ብዬ መመለስ እንዳለብኝ የማስብበት ጊዜ ሊሰጠኝ አይገባም? እኔ እኮ አባቴን በማጣት የተጎዳው ሰው ነኝ፡፡ ሌላ ሰው ለማጣትም ሆነ ከእሱ ጋር በዚህ ሁኔታ ተቀራርቦ ለመራራቅ ዝግጁ አልነበርኩም” ብላ በረጅሙ ተንፍሳ እንባዋን እየጠራረገች “ወይ አደይ ገረመው ….ይኼኔ እኮ እሱ በሰላም ተኝቷል እኔስ? ….እኔ ምን እያረኩ ነው?” ብላ በድጋሚ የወረደ እንባዋን ጠራርጋ አልጋዋ ውስጥ ገብታ ተኝታም ያለማቋረጥ የሚወርድ እንባዋን ከስር ከስር እየጠረገች ፈገግ ብላ “ለምንድነው በረሃ ላይ ብቻውን እንደተጣለ ሰው የማውቃቸው ሰዎች ሁሉ እየናፈቁኝ እና ብቻውን እንደቀረ ሰው እየተሰማኝ ያለው” ብላ በአቶ እንቁ ፈገግ ብለው በቀሩ አይኖቻቸው መታየት እና ምንም ሳይናገሩም ሳይንቀሳቀሱም ፍቅር በሚሰጡበት መንገድ ይኼ መጥፎ ስሜት እንደሚቀላት ስለምታውቅ ሲነጋ አቶ እንቁ ጋር ለመሄድ ወስና ተኛች፡፡

ከመፅሐፉ የተወሰደ

Post a Comment

0 Comments